top of page

ከእውነት ጋር - ከፍትህ ጋር - ከነፃነት ጋር ምንጊዜም መቆም አለብን::

Updated: Jun 26, 2020



በዚህ በተሰደድንበት ሰሜን አሜሪካ በዘርና በቀለም ወይም በተለያየ መንገድ ሲካሄድ የቆየው የጥላቻና የማጥቃት ተግባር እጅግ አሰቃቂ መልክ አለው:: ከአገራችን ርቀን ከመንግሥት እሥርና ግድያ ሸሽተን ስንሰደድ ይህ አገር ሰርተን እንድንኖርበት ልጆቻችንን እንድናስተምርበት ያመቻቹልን የሞቱልን የተሰውሉን ብዙ ጥቁር አሜሪካኖችና ሌሎች ዘሮችም ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ ብዙ አሉ:: ይሁን እንጂ ይህ ግፍና በደል በተለያየ መልኩ በየምንኖርበት አካባቢ ዛሬም አለ:: ዓይናችንን ከፍተን ብናስተውል በየእለት ኑሮአችን በየምንኖርበት አካባቢ ሲፈፀም ይስተውላል:: ከልጆቻችን የትምህርት ገበታ / በየምንሰራበት ሥፍራ/ በምንኖርበትና በምንገበያይበት አካባቢ ዕለት በዕለት የጥላቻና የንቀት ድርጊቶች ይካሄዳሉ:: 

እውቀታችን በንግግራችን የሚፈረጅበት ምድር ነው:: ይህ በአሰቃቂ የፓሊስ የጥላቻ ድርጊት ሕይወቱን ያጣው George Floyd እንደሌሎቹ ጥቁሮች በቆዳው ቀለም ምክንያት ብቻ ነው:: በአሜሪካን 75 ከተሞችና በመላው ዓለም ቁጣና እንቢተኝነትን  ያስነሳው ዛሬም በዚህ ዘመን ላይ ይህን ዓይነት ፅዩፍ ድርጊት እየተካሄደ ስላለ ነው:: የዚህ ቆራጥ ትግል ውጤት ደግሞ እየታየና እኛም ታሪክን ለመመስከር መታደላችን ነው:: ያለአንዳች የቆዳ ቀለምና የዘር ልዩነት የሰብአዊነትን ጥያቄ የሚቀበል ሁሉ በአንድነት ተጣምሮ የተነሳበት ነው:: ዓለም በከፍተኛ የሥልጣኔ ደረጃ ላይ ደርሳለች በምንልበት ዘመን ይህን መሰል በጥላቻ ላይ የተመሰረተ በምንም መልኩ የሚካሄድ እንቅስቃሴና ድርጊት መገታት አለበት:: መተካት የማንችለውን የሰውን ልጅ ነፍስ የማጥፋት መብት የለንም:: 

እግዚአብሔር  ሰውን በአምሳሉ ፈጠረ ብሎ የሚያምን ሁሉ ፍጡርን በእኩልነት የማየት ግዴታ አለበት:: ከዚህ ሃሳብ የተለየ ድርጊትን የሚፈፅም ከፈጣሪው የተጣላ ከእምነቱ የራቀ ብቻ ነው:: ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ላይ ውሎ የሰውን ልጅ ሐጢያት በደሙ ያጠበው ያፀዳው በቀለም በዘር በቋንቋ ሳይከፋፍል ለመላው ፍጥረቱ ሲል ነው የተሰዋው:: እያንዳንዳችን በተለያየ መንገድ የምናሳየው  የመጎዳዳትና የመጠፋፋት ተግባር ከእምነታችን ጋር የማይጣጣም ነው:: 

ከእውነት ጋር - ከፍትህ ጋር - ከነፃነት ጋር ምንጊዜም መቆም አለብን:: 


Comments


bottom of page